(ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ. /LFSDP/እንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት)፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት  የተሳተፉ  አረሶ አደሮች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ 28 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ ሰሞኑን ከፌደራል የተውጣጡ የእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ከፍተኛ ባለሞያዎች ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው የክልል ወረዳዎች ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት ላይ በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሙሉጌታ እንደተናገሩት ከሆነ ፕሮክቱ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአርሶ አደሮች ህይወት እየተለወጠ መጥቷል።

እንደ ዋና አስተባባሪው ማብራሪያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአራቱም እሴት ሰንሰለት ላይ ተደራጅተው በስራ ላይ ያሉ 547 የጋራ ፍላጎት ቡድኖች 19.1 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝተዋል፡፡

በተመሳሳይ ወራት ጊዜ ውስጥ  በአራቱም እሴት ሰንሰለት በተለያየ ጊዜ ተደራጅተው በሰራ ላይ የሚገኙ 37  ህብረት ሥራ ማህበራት ያመረቱትንና ያሰባሰቡትን ምርት ለገበያ በማቅረብ  8.9 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘታቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።

በዚህም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የተሻለ ገቢ በማግኘት የተሻለ የኑሮ ዘይቤ እየተከተሉ መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ የራሳቸውን ኑሮ ከማሻሻል በተጨማሪም ለአካባቢው ማህበረሰብ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት የገበያ ማረጋጋት ስራ እየተወጡ መሆናቸውም ተነግሯል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ዶ/ር ቶማስ ቸርነት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በቀጣይም በክልሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩ ሲሆን በሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ መንገድ በመተግበር ላይ መሆኑን አንስተዋል።

ዶክተር ቶማስ ይህ ፕሮጀክት እንደ አገር የተያዘውን የሌማት ቱሩፋት በተሳካ መንገድ ይተገበር ዘንድ ፕሮጀክቱ የጎላ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

አስተባባሪው በተለይ በወተት ልማት፣በዶሮ እርባታ፣በቀይ ስጋ፣በዓሳ  ምርት እና በእንስሳት ጤና  ላይ የተጠናከረ ስራ በመስራት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሻሻል ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

error: Content is protected !!