በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት ከጋምቤላ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ቢሮ ጋር በመተባበር ከታህሳስ 12 እሰከ 13፣2013 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት የቆየ የዓሣ ምርት ማሻሻያ ላይ ያተኮረ ስልጠና በጋምቤላ ከተማ ተሰጠ፡፡
በስልጠናው ላይ የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት በለሙያዎች እና በእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት የታቀፉ በጋራ ፍላጎት ቡድን የተደረጁ /Common Interest Group/ ተጠቃሚ አርሶ/አርብቶ አደሮች እና ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የአቅም ግንባታ ስልጠናው ዋንኛ ትኩረት የነበረው በተፈጥሮ ውሃ አካለት የዓሣ፣ ማስገር፤ የዓሣ ድህረ ምርት አየያዝ እና ዝግጅት እንዲሁም በዓሣ ምርት ጥራት አጠባበቅ ላይ ነው፡፡
የጋምቤላ ክልል የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ብሩ የስልጠናውን አስመልክተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት በክልሉ አቦቦ ወረዳ ስራውን ከጀመረ ጊዜ ወዲህ ወጣቶችን፤ ሴቶች፤ አነሰተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው አርሶ/አርብቶ አደሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በዓሣ ማስገር፤ በዶሮ እርባታ እና በእንስሳት ማድለብ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲችሉ አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኘሮጀክቱ ስራ በጀመረባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የዓሣ ማሰገር ስራ እና ምርት ተረክበው የሚሸጡ 120 ማህበራትን ለማደራጀት ታቅዶ 30 ማህበራትን በማደራጀት ስራውን እያከናወኑ እንደሚገኙ ም/ቢሮ ሃላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የክልሉ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ልማትን ለማጠናከር በዞን፤ በወረዳ እና በቀበሌዎች ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ የቤተሰብ የገቢ ምንጭን ለማሳደግና ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ ከፍተኛ ስራ እንደሚጠበቅባቸው ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል ፡፡
በሌላ በኩል በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ኘሮጀክት ከፍተኛ የዓሣ እስፔሻሊስት በላሙያ አቶ ቢምረው ታደሰ የስልጠናውን ፋይዳ አስመልክተው በሰጡት አስተየያት በጋራ ፍላጎት ቡድን የተደረጁ /Common Interest Group/ አርሶ/አርብቶ አደሮች እና ወጣቶች ያላቸውን የአቅም ክፍተት በመለየት የዓሳ ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ፤ የምርት ጥራቱን በአግበቡ በመጠበቅና ብክነት በመቀነስ አዘጋጅተው ለተጠቃሚው በማቅረብ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያሥችል መሆኑንን ጠቅሰው በቀጣይም የአቅም ግንባታ ስልጠናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
በገምቤላ ክልል በአቦቦ ወረዳ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት አስተባበሪ አቶ ኡሞድ ኡኮንጎ እንደገለጹት በክልሉ በአቦቦ ወረዳ ሰላሳ የተለያዪ በጋራ ፍላጎት ቡድን የተደረጁ /Common Interest Group/ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሃያ አምስቱ በዓሣ ማስገር ማህበራት የተደረጁ ሲሆን ቀሪው አምስቱ በዓሣ ግብይት የተደራጁ ናቸው ብለዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በወረዳው 425 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በጋራ ፍላጎት ቡድን የተደረጁ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 80 ዎቹ ሴቶች ሲሆኑ 347ቱ ወንድ አርሶ/አርብቶ አደሮች እና ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በተያዘው በጀት ዓመት 90 በጋራ ፍላጎት ቡድን የተደራጁ አባወራ እና እማወራ እንዲሁም ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት በቅርቡ ወደ ስራ ለማስገበት የቅድመ ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን የክልሉ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት አስተባባሪ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በስልጠና ላይ ተሳታፊ የነበሩ ከአቦቦ ወረዳ እና ከመንደር 17 የመጡ አቶ ኡቻንግ አቡር እና አቶ ኦቦንግ አጎዋ ኦኬሎ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ስልጠና አግኝተው እንደማያውቁ እና ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ እና በተለይ ተደራጅተው ወደ ስራ ለመግባት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ለአርሶ/አርብቶ አደሮቸ እና ለወጣቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ እና የክህሎት እና የግንዘቤ ክፍተት ለመሙላት እየሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተነሳሽነታቸውን እንደሚጨምርላቸው ተናግረዋል ፡፡
በጋምቤላ ክልል የኤልዊሮ ግድብ 74.6 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን የግድቡ ከፍታም 22 ሜትር ነው፡፡ በክልሉ 80 በመቶ የዓሣ ምርት ከኤልዊሮ ግድብ የሚገኝት ሲሆን ቀሪው 20 በመቶ ከባሮ ወንዝ ነው፡፡ በክልሉ 2010 ዓ.ም አካባቢ በውሃ እና በውሃ አካላት ላይ በተደረገው ጥናት መሠረት በዓመት ከ15 ሺህ እስከ 17 ሺህ ቶን የዓሳ ምርት እንደሚመረት ከክልሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡