በወተት ልማት ሴክተር ላይ የሚታዩትን ችግሮች በመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ ድርሻ መኖሩን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘውና በአለም ባንክ የሚደገፈው የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት (LFSDP) ብሄራዊ የወተት ሀብት ልማት ኘሮግራም ሰሞኑን በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በአደአ በርጋ የወተት ከብቶች ንዑስ ማዕከል በይፋ አስጀምሯል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ዑመር ሁሴን በቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከያዘው የ10 ዓመት የእቅድ መርሃ ግብር ላማሳካት ካቀደው ውስጥ አንዱ የሆነው የእንስሳት ዘርፍ ልማትን ሲሆን በተለይም በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉትን ማለትም የእንስሳት መኖ ልማት ዝርያን ማሻሻልና በእንስሳት ጤና ላይ መሠረታዊ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት እና በምርምር በመደገፍ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡
በቀጣይ አርሶ አደሩ ከአገር በቀል የእንስሳት ዝርያ ወደ ተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያ በማሸጋገር እና ከእንስሳት ልማት ዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ከፍተኛ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአሁን ጊዜ 200 ዝርያ ያላቸው የቦረና ዝርያ ጊደሮች እና 100 የሚሆኑ የፎገራ ዝርያ ቻግኒ የተሻሻሉ ጊደሮችን እንዳስገባና በቀጣይ ሦስት ዓመት ውስጥ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አርሶአደሩ
ከእንስሳት ምርት እና ምርታማነቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምርጥ ዝርያዎችን የማስፋፋት ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም በአሁን ጊዜ በደቡብ ክልል በከምባታ እና ጠምባሮ እንዲሁም በሲዳማ ክልል የተሻሻሉ የእንስሳት ልማት ዘርፍ ላይ እየታዩ ያሉት ምርጥ ተሞክሮዎችን የሚያበረታታ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ከፈና ኢፋ የማዕከሉ ተግባራትን ክንውኖች አጠቃላይ እንቅስቃሴውን አስመልክተው ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፍ የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በኢንስቲትዩት ሥር ከሚገኙት 20 የፌዴራል ማዕከላት አንዱ ሲሆን ደጋማውንና መካከለኛ ደጋማ የአየር ንብረት አካባቢዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን ከ200 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ የሚገኝና ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ በማስገባትና በማላመድ ለሀገራችን ተስማሚ የሆኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨት ለባለድርሻ አካላትና ለአርሶ አደሮች ማስተዋወቅ እንዲሁም ብሔራዊ ፕሮግራሞችንና ኘሮጀክቶችን በማስተባበር በተለይም አርሶ አደሩ ዘንድ የሰርቶ ማሳያ ሥራዎችን በሰፊው በማከናወን በተጠቃሚው ዘንድ ፍላጎት በመፍጠር የተለያዩ የላብራቶር ትንተና አገልግሎቶችን የአፈር፤ የመኖ ይዘትና የወተት ቴክኖሎጂ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከብሔራዊ እና አለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር በትብብር በመስራትና ምክረ ሀሳቦችን በመስጠት አንጋፋ ተቋም መሆኑን የማእከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ከፋና ኢፋ በወቅቱ ባቀረቡት ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡
በተለይም የምርምር ማዕከሉ የትኩረት ዘርፎች መካከል የሰብል ምርምር /Field crops and Horticultural/ የእንስሳት ምርምር ወተት፣ መኖ ልማት የሥነ ምግብ እና ጤና፣ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና ጥበቃ የማህበረሰብ ሳይንስ የግብርና ምጣኔ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሰብል ጥበቃ ስራዎች ላይ እየሰራ ይገኛል:: በሆለታ ግብርና ምርምር እስከ አሁን ድረስ ከ132 በላይ የተለዩ የሰብል ዝርያዎች በምርምር መገኘቱ በወቅቱ ባቀረቡት ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡