በግብርና ሚኒስቴር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት (LFSDP) ጋር በመተባበር የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎን ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ውይይቱ ሴቶች እና ወጣቶች በግብርና ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ ግንዛቤን ይፈጥራል ተብሏል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት አየለ በበኩላቸው በውይይት መድረኩ ላይ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር ላይ እንደተናገሩት ሴቶች በግብርናው ኢኮኖሚ ላይ እንዲሁም በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ላይ ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡
በተለይም የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎን በማሳደግ ሴቶች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በግብርና ልማት ዘርፍ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የበለጠ በማጉላት ከክልሎች ጋር በቅንጅት በርካታ ስራዎችን መስራታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም በተያዘው የ10 ዓመት የእቅድ ፕላን በግብርና ኢኮኖሚ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች ጋር እኩል ድርሻ እንደሚኖራቸው እና በተለይ በአሁን ጊዜ ሴቶች በእንስሳት ልማት ዘርፍ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ ከእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት እና ከክልሎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ወ/ሮ ትዕግስት ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ቶማስ ቸርነት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የሴቶች እና የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎን ለማሳደግ ፕሮጀክቱ እየተገበረ ባለው 6 ክልሎች እና 58 ወረዳዎች እንዲሁም 1755 ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ እና በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እደሚቀጥል ዶ/ር ቶማስ አስረድተዋል፡፡ የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት በአራት የእንስሳት እሴት ሰንሰለት ላይ የሚሰራ ሲሆን በወተት፤ በዓሣ ሀብት፤ በቀይ ስጋና በዶሮ እርባታ ላይ ከ10,560 በላይ በጋራ ፍላጎት የተደራጁ አባወራ እና እማወራዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡