አዲስ አበባ (LFSDP) ህዳር 28/2015 የወተት ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተሻሻሉ የላም ዝርያዎችን በማዳቀል ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ እንደሚገኝ የሶዶ ዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል ገለጸ።
የሶዶ ዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል ኃላፊ ምህረቱ ማርቆስ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ውጤታማ የእንስሳት ዝርያዎችን በማሻሻል የአርሶ አደሩን የወተት ላም ተደራሽነት እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።
የአርሶ አደሩን የወተት ሃብት ልማት ተደራሽነት ለማሳደግም ለቃሊቲ፣ ለነቀምት እና ለሀዋሳ ዘርያ በማቅረብ በሰው ሰራሽ የማዳቀል ዘዴ ውጤታማ የወተት ላሞችን ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ጀርሲ የተሰኙ ንጹህ የውጭ ዝርያ ያላቸውን ላሞች ኮርማ እንዲያመርቱ፤ የቦረና ላሞች ደግሞ ውጤታማ የወተት ጊደር እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
እየተካሄደ በሚገኘው ውጤታማ የወተት ላም ዝርያ ማሻሻያ ሥራም ለሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እና አቅራቢያው ላሉ አርሶ አደሮች ነፃ የማዳቀል አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ማዕከሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአርሶ አደሩን የወተት ላም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በማዕከሉ የሚገኙ የጀርሲ ዝርያዎችን ለኮርማነት፣ የቦረና ላሞችን ደግሞ ጊደሮችን እንዲሰጡ በማድረግና ለሥርጭት በማዘጋጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እየተከናወነ የሚገኘው ውጤታማ የወተት ላም የማዳቀል ማሻሻያ ሂደትም የአገር ውስጥ ላሞች የሚሰጡትን የወተት ምርት ወደ 50 በመቶ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል።
ሂደቱም ውጤታማ የወተት ምርት ሰጪ ከሆኑና ንጹህ የውጭ ዝርያ ካላቸው ላሞች ጋር እየተካሄደ እንዳለም ጠቅሰዋል።
ማዕከሉ የኢትዮጵያዊያንን የወተት ፍላጎት ለማሳደግ ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ የወተት ላሞችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
99 የቦረና ጊደሮችን ወደ ማዕከሉ በማስገባት የተሻሻሉና ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ሴት የወተት ጊደሮች እንዲወለዱ በማድረግ ለአርሶ አደሮች እንደሚያሰራጭ ጠቅሰዋል።
እየተካሄደ የሚገኘው የወተት ላም ዝርያ የማዳቀልና የማሻሻል ሥራም ገበያ ላይ እየጨመረ የመጣውን የወተት ላም ፍላጎትና የዋጋ ንረት በማረጋጋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ለማዕከሉም የፌደራል የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት የቦረና ጊደሮችን በመግዛት፣ የመኖ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ፣ የእንስሳት አያያዝ አቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት፣ የእንስሳት ሕክምና እና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሶዶ ዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል በ1963 ዓ.ም 35 የሆሊስቴይን ጊደሮችን እና 22 የሆሊስቴይን ኮርማዎችን በመያዝ “ዋዱ” በሚል ፕሮጀክት ተቋቁሟል።