አዲስ አበባ (LFSDP) 2/ 06/2015 በሰብል ምርታማነት እየተመዘገበ ያለውን ስኬት በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ያላት አገር ብትሆንም ከዘርፉ በሚገባት ልክ ሳትጠቀም ቆይታለች፡፡

በመሆኑም መንግሥት በተለይ በስንዴ ልማት ላይ በአጭር ጊዜ ያስመዘገበውን ስኬት በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ላይ ለማስቀጠል እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮችን፣ ሥራ አጥ ወጣቶችንና ሴቶችን በማደራጀት ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ሲሆን፤ በዚህም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ሥራ ፈጠራ እና  የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቅርቡ በተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የወተት፣ የሥጋ ዶሮና እንቁላል፣ የማርና የዓሳ ምርታማነትን በማሳደግ የተመጣጠነ የስነ-ምግብ ሥርዓት እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የአገር ውስጥ የላም ዝርያዎች በሰው ሰራሽ ዘዴ ከውጭ ከመጡ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል በቀን እስከ 15 ሊትር ወተት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በአገር ውስጥና በተሻሻሉ የላም ዝርያዎች መካከል ያለውን የወተት ምርት ልዩነት ለማጥበብም በሰው ሰራሽ የማዳቀል ሥርዓት የወተት ላሞችን የማባዛት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል

ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ በማስገባትና በሰው ሰራሽ የማዳቀል ሥርዓት ሴት ጥጆችን መውለድ የሚያስችል የማዳቀል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በሚኒስቴሩ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት፤ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ከ10 ሺህ በላይ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ሥራ አጥ ወጣቶች፣ ሴቶችና አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮች በማደራጀት በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮቹ ከራሳቸው አልፎ ለየአካባቢያቸው ነዋሪዎችም የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የወተት ምርታማነትን ለማሳደግም የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ላሞች በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ በአገር አቀፍ ደረጃ እያከናወነ ባለው የልማት ሥራም በአጠቃላይ ከ120 ሺህ በላይ ዜጎችን በቀጥታ፤ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎችን ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የወተት ላሞችን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ሥራም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡

ዘጋባው Lfsdp.com

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

error: Content is protected !!