የአልዌሮ ግድብ እና ሌሎች ውሃማ አካላትን በመጠቀም በተከናወነ ሥራ በዓሣ ልማት ዘርፍ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የጋምቤላ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ
(ግንቦት 07 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ).የአልዌሮ ግድብ እና ሌሎች ውሃማ አካላትን በመጠቀም በተከናወነ ሥራ በዓሣ ልማት ዘርፍ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የጋምቤላ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
የጋምቤላ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ብሩ በክልሉ የእንስሳት እና ዓሳ ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት በ2012 ዓ.ም በክልሉ ከሚገኙ ሦስት ዞኖች መካከል አንዱ በሆነው አኝዋክ ዞን አበቦ ወረዳ ውስጥ መጀመሩን ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ ከሆነ መጀመሪያ 180 የጋራ ፍላጎት ያላቸውን ተጠቃሚ ቡድኖች(CIG) በማደረጃት ስራ መጀመሩን አብራርተዋል።
አቶ ደሳለኝ ለእነዚህ ተጠቃሚዎች በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ልማት ዘርፍ ብሔራ ማስተባበሪ በዓሳ ማስገር ዘርፍ ላይ ከስልጠና ጀምሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል ፡፡
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ውጤት መመዝገቡን ተናረዋል። በዚህም ቀደም ሲል በጋራ ፍላጎት የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች ወደ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት መሸጋገራቸውን አስረድተዋል።
እነዚህም 180 ቡድኖች አሁን ላይ በውስጣቸው ከ25 እስከ 50 የሚደርሱ የጋራ ፍላጎት ያላቸው አባላትን በማካተት አደረጃጀቶችን በመያዝ ወደ አምስት ማሕበራት መሸጋገራቸውን ጠቅሰዋል።
በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን የአበቦ ወረዳ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ኡመድ ኦኮንጎ በበኩላቸው 411 ተጠቃሚዎችን ያካተቱት አምስቱ ማህበራት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ኡመድ እንደሚናገሩት አምስቱ ማሕበራት አሁን ላይ በቀን እስከ ስድስት መቶ ኪሎ ግራም ዓሳ እያመረቱ ነው።
ይህ ምርትም አብዛኛውን ጊዜ ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን በዚህም በየጊዜው በሚካሔድ ሽያጭ ገቢያቸው እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ውጤት መብቃት የተቻለው በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ልማት ዘርፍ ብሔራ ማስተባበሪ ባደረገልን ልዩ ክትትል እና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ነው ብለዋል።
የአቦቦ ወረዳ መንደር 17 አልዌሮ ግድብ አካባቢ ኗሪ የሆኑት ወጣት አጀንዳ ኡጁሉ እና ወጣት ዳክ ውጉዱ ለበርካታ ዓመታት ኑሯቸውን ሲገፉ የኖሩት ከጉማሬ እና አዞ ጋር በመጋፋት እና ለህይወታቸው እጅግ አደገኛ በሆነው ባህላዊ ዓሳ ማስገር ስራ ላይ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየሆነ ያለው እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት ወደ አበቦ ወረዳ ሲገባ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የህይወት ዘይቤያቸውን እንደለወጠዉ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ወጣት አጀንዳ ኡጁሉ እና መሰሎቹ በአልዌሮ ግድብ ላይ የጥንቷን መናኛ መንጠቆ ሳይሆን በፕሮጄክቱ ድጋፍ በተገዛው ዘመናዊ ዓሳ ማስገሪያ በመጠቀም ከእለት ጉርሳቸው ባለፈ ለአካባቢው ገበያ በቂ የሆነ የዓሳ ምርት እያቀረቡ ይገኛሉ።
በአበቦ ወረዳ የተደራጁት የእነ አጀንዳ ኡጁሉ እና አጋሮቻቸው አምስት ማህበራት በቀን 500 እስከ 600 ኪሎ ግራም ጥራቱን የጠበቀ ዓሳ እያመረቱ ይገኛሉ።
አልዌሮ ግድብ እና ከሌሎች የክልሉ የውኃማ አካላትም በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ጠቀሜታ ለመስጠት ሁኔታዎች ምቹ እንዲሆኑ በፊደራል ደረጃ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብሄራዊ ማስተባበሪያው አረጋግጧል።
በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ወንዞች እና ውሃማ አካላት በአጠቃላይ በዓመት ከ15 ሺህ እስከ 17 ሺህ ቶን የዓሳ ምርት እንደሚመረት ከክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ልማት ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል