( ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ): በአስደማሚው የአካባቢ  ጥበቃ በሆነው የእርከን ሥራቸው   ይታወቃሉ፣ኮንሶዎች ። አሁን ግን እነዚህ የኮንሶ አርሶ አደሮች ሌላ ዘርፍ መለያቸው እየሆ መጥቷል፣ የዶሮ እርባታ ልማት ።

ድርቅ በተደጋጋሚ የሚጎበኘው ይኸ አካባቢ  አርሶ አደሩ የእንስሳት ሀብቱን በተለይም የዶሮ  ሀብቱን እንዲጠቀም ጠንካራ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት  ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት(LFSDP) ድጋፍ በተገነባው እና ከሰባት ሺህ አምስት መቶ በላይ የዶሮ ጫጬቶች በሚረቡበት በእነ ኩኢሳ ደጊ የዶሮ እርባታ ማኅበር ተገኝተናል።

ኮይሶ ደግሞ አንድ መቶ አባላት ያሉት  የማኀበሩ ሰብሳቢ ነው ። እነዚህ ዶሮዎች የሥጋ እና የእንቁላል ናቸው ። ጤና ባለሞያ :እና ፕሮጀክት አስተባባሪ አለው የማኀበሩ ። በየጊዜው ሥልጠና እንደሚሰጥ አስተባባሪው በጉብኝታችን ወቅት ገለጻ አደርጎልናል ::

ምግብ በቀን ሦስት ጊዜ እንደሚሰጡ ተናግሯል ።  በየቀኑ ክትትል እንደሚደረግላቸውም አስተባባሪው ተናግሯል ።  ከእዚህ እና ሌሎች ማኀበራት ዶሮ ለአካባቢው ማኀበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ይሰራጫል።

ወ/ሮ ካሰች ገልቦ የመንግሥት ሠራተኛ እና የሁለት ልጆች እናት ናቸው።  በግቢያቸው የሚገኙት ዶሮዎች ደግሞ  የቤተሰባቸው የእንቁላል ምንጭ ናቸው ። አንዷ ልጃቸው ኬጂ የምትማር ሲሆን ሁለተኛዋ ደግሞ አመት ከሁለት ወር እንደሞላት ወ/ሮ ካሰች ገልጸውልናል።

ከሚያረቧቸው ዶሮዎች የሚገኘውን እንቁላል ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ ለመስጠት እየረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይኸም ልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ አደርጓቸዋል።

የኮንሶ ዞን አሁን በሰፊው በዶሮ ሀብቱ ተጠቃሚነቱ እያደገ መሆኑን በዞኑ ግብርና መምሪያ እንስሳት ዘርፍ ኃላፊው አቶ ዮሐንስ ኩስያ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዶሮዎች እንዳሉ ነግረውናል። በዚህም የእንቁላል ምርቱ  ያለ ገበያ ችግር ወደ አጎራባች አካባቢዎች አለፍ ሲልም እስከ ኬንያ እንደሚደርስ ገልፀዋል።

ኃላፊው ከፌደራል ግብርና የዘርፉ ፕሮጀክት በሚደረገው ድጋፍ የዶሮ እርባታ በጣም አዋጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።  አርሶ አደሮች በከፍተኛ ደረጃ  ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውንም ገልፀዋል ።

ይህ በዓለም ባንክ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወነው የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ልማት የኮንሶ አርሶ አደሮችን ብቻ ሳይሆን በሰባት ክልሎች በ58 ወረዳዎች አንድ ሺህ ሰባት መቶ አምሳ አምስት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ጭምር ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሌማት ቱርፋት መርኃ ግብርን ባስጀመሩበት ወቅት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ራስን መቻል ጉዳይ ኢትዮጵያ ካረጋገጠች በሀገር ደረጃ ያለው በምግብ ራሰን የመቻል ሩጫ በቀላሉ የሚሳካ ሲሆን ለቀጣዮች አራት ዓመታት ይህንን በማሳካት ዶሮ፣ ስጋ፣ ወተት፣ ማር እና አሳን  ማትረፍረፍ እንችላለን ማለታቸው ይታወሳል ።

ታዲያ የኢትዮጵያን የድህነት ታሪክ ይቀይራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሌማት ቱርፋት በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ከ11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት፣ ከ3 እስከ 9 ቢሊዮን የሚገመት እንቁላል እንዲሁም ከ90ሺሕ ቶን እስከ 204 ሺሕ ቶን የዶሮ ስጋ ለማምረት እና ገበታን በተመጣጠነ ምግብ ለመሙላት ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ ያለው  የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክትም ይህን አገራዊ ዕቅድ በማሳካት ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ። የኮንሶ ዞን የእንስሳት ሀብት  አስተባባሪም ይህን አረጋግጠውልናል።

 

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

error: Content is protected !!