ግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት በወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን በማቀነባበር እና በመሸጥ ላይ ለተሰማሩ የህብራት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች የወተት ማቀዝቀዣ የተገጠመለት ማጓጓዣ መኪናዎችን ለ 4 ክልሎች ለኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ለሲዳማ ክልሎች ርክክብ አደረገ፡፡
በወተት አመራረት ረገድ በ2015 በጀት ዓመት የተደራጁ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች እና የህብረት ስራ ማህበራት በአጠቃላይ ከ36 ሚሊዩን ሊትር በላይ ወተት ማምረት መቻላቸውን ተገልጿል፡፡ በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ፍቅሩ ራጋሳ (PhD) በርክክቡ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራችን ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ክምችት እና ለወተት ልማት አመቺ የሆነ ስነ-ምህዳር የላት ሲሆን ከዚህም ውስጥ የወተት ከብት ከፍተኛ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን የግመል እና የፍየል ወተት በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢ በስፋት እንደሚመረት ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት የአገራችን አጠቃላይ አመታዊ የወተት ምርት በ2015 ዓ.ም 8.6 ቢሊዮን ሊትር እንደሆነ የግብርና መረጃ የሚያሳይ ቢሆንም የድህረ ምርት አያያዝና የግብይት ትስስሮች በቂ ባለመሆናቸው በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ ምርት ቢኖርም በገበያ እጦት ምክንያት ለብክነት ሲዳረግ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ዝቅተኛ አቅርቦት እና ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ዶ/ር ፍቅሩ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በአሁን ጊዜ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል እንደ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በሌማት ትሩፋት ኘሮግራም የወተት መንደር በመመስረትና ለትግበራውም አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዝርያ ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የሰው ሰራሽ ማዳቀል አገልግሎት በስፋት በወተት መንደር የታቀፉ አርቢዎችን በማሰልጠን አዳቃይ ቴክኒሻኖችን ክሎት እንዲያዳብሩ እየተደረገ እንደሚገኝም ሚኒስቴር ዴኤታው ጨምሮ አስረድተዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስቴር ግርማ አማንቴ / PhD/ በበኩላቸው እንደተናገሩት የሌማት ትሩፋቱን መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ አጠቃላይ ሀገራዊ የወተት ምርትን አሁን ከደረሰበት ወደ11 ቢሊዮን ሊትር ለማድረስ ከክልሎች እና ከባለድርሻ አከላት ጋር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ይህንንም እቅድ እውን ለማድረግ የልማት ኘሮጀክቶችንና አጋር ድርጅቶችን በማቀናጀትና በማስተባበር ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ኘሮጀክቶችም እውቀታቸውንና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ረገድ የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ልማቱን ለማፋጠን የበኩለቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ ጠቁመዋል፡፡
የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት (LFSDP) ከዓለም ባንክ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከተጠቃሚዎች በተገኘ 176 ሚሊዮን የአሜርካ ዶላር በጀት በ 7ክልሎች፣ በ58 ወረዳዎች እና 1755 ቀበሌዎች እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን በኘሮጀክቱም 10 ሺህ 333 የጋራ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች (1428 በወተት ምርት ላይ የተሰማሩ)፣ 294 የህብራት ስራ ማህበራት (59 የወተት ህብረት ስራ ማህበራት) እንዲሁም 39 ዩኒኖች (15 በወተት ግብይት እና ማቀነባበር ላይ የተሰማሩ) በመደገፍ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ 10 ሺህ ሊትር ወተት በአንድ ጊዜ መያዝ የሚችል 7 የወተት ማጓጓዝ መኪናዎችን ኘሮጀክቱ በ 606,586 የአሜሪካ ዶላር ወጪ በማድረግ ከውጭ አገር በማስገባት ለተመረጡ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በክልሎች አማካኝነት ለማድረስ ታስቦ የተዘጋጀ ኘሮግራም መሆኑ ተገልጿል፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች እንደየ ክልሎች የማምረት አቅም ለአማራ 2 ለኦሮሚያ 2 ለደቡብ 2 እና ለሲዳማ 1 የተመደቡ ሲሆን፤ ተሽከርካርዎቹን ለተመረጡ የወተት ማህበራት በማሰረከብ በአፋጣኝ ወደ ስራ እዲገቡ እና ውጤታማነታቸውንም እንዲከታተሉ በተለይም ከወተት ማሰባሰቢያ ወደ ማቀነባባርያ እና ማከፋፈያ ቦታዎች በማጓጓዝ የወተት ጥራት ደህንነትንና የድህረ ምርት አያያዝ በማሻሻል ተጠቃሚው ህብራተሰብ ተገቢው አገልግሎት እንድያገኙ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስቴሩ አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም በግብርና ሚኒስቴር፣ በተጠሪ እና በባለድርሻ ተቋማት መካከል ጥሬ ወተት ማጓጓዣ (Raw Milk Cold Chain Truck) ተሸከርካሪ ለማስተላለፍ የተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ ውል ስምምነት ተካሂዷል፡፡