( 5/01/2016 እንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት ) በግብርና ሚኒስቴር እንስሳት ዓሣ ዘርፍ ልማት ድጋፍ በአገር አቀፍ ደረጃ በወተት ከብቶች የሥነ- ተዋልዶ ባዮቴክኖሎጂ ዘዴዎች አተገባበር መመሪያ ላይ በኦሮሚያ ክልል በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ከ04-05/01/2016 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው የጋራ ውይይት መድረክ ተጠናቀቀ፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወተት ሀብት ልማት ዴስክ ሀላፊ አቶ ለማ ገመዳ የተካሄደውን የሁለት ቀናት ውይይት አስመልክተው በሰጡት አስተያዬት ባለፉት 6 ወራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሰነድ ዝግጅት ላይ እንደ ነበር አብራርተዋል።
የተዘጋጀው ሰነድ ከዚህ በፊት በእንስሳት ልማት ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ በዝርያ ማሻሻል ፣በመኖ ልማት፣በእንስሳት ጤና እና የአዳቀይ ቴክንኒሸያን ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳል።
ከኦሮሚያ ክልል ከ6 ዞኖች እና 12 ወረዳዎች የተውጣጡ የወተት እርባታ ባለሙያዎች፣የእንስሳት ጤና ባለሞያዎች፣ የአዳቃይ ቴክኒሸያን ባለሙያዎች ፣ የመኖ ልማት ባለሙያዎች በአጠቃላይ 94 ተሳታፊዎች በሰነዱ ላይ ውይይት አድርገዋል።
ከባለሞያዎቹ በተጨማሪ በሰነዱ ላይ የዪኒቨርሲቲ ምሁራን እና የዘርፉ ተመራማሪዎች እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ፣ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ የኘሮጀክቱ ተወካዮች ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ አማካሪ አቶ ግርማ ሙሉጌታ በበኩላቸው ግብርና ሚኒስቴር በአሁኑ ጊዜ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል እንደ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሌማት ትሩፋት ኘሮግራም የወተት መንደር በመመስረትና ለትግበራውም አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዝርያ ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የሰው ሰራሽ ማዳቀል አገልግሎት በስፋት እተሰራበት ነው ብለዋል። በወተት መንደር የታቀፉ አርቢዎችን በማሰልጠንና አዳቃይ ቴክኒሺያኖችን ክሎት እንዲያዳብሩ እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል ፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዘርፉ ምሁራን እና ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡት ባለለሙያዎች መንግስት ለእንስሳት ልማት ዘርፉ እንደ በጋ ስንዴ ልማት ሁሉ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አንስተዋል።
አርሶ አደሮቹ ከባህላዊ የአረባብ ዘዴ ተላቆው በዘመናዊ የአረባብ ዘዴ እንዲከተሉ ማድረግ እና አርሶ አደሮቹም ከእንስሳቱ ምርት እና ምርታማነት የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይገባል ነው ያሉት።
በተዘጋጀው አገር አቀፍ በወተት ከብቶች የስነ – ተዋልዶ ባዮቴክኖሎጂ አተገባባር መመሪያ ሰነድ ላይ በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጧል።
በግብርና ሚኒስቴር በዓለም ባንክ የሚደገፋው የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ኘሮጀክት (LFSDP )የእንስሳት ዓሣ ልማት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል። (ዘጋባው LFSDP.COM ነው)