(መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ;LFSDP)፡ በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ በዶ/ር ዮሃንስ ግርማ  የተመራ ልዑካን ቡድን ሰበታ በሚገኘው የብሔራዊ ዓሣና የውኃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ጉብኝት አድርጓል።

በጉብኝቱ ወቅት የብሔራዊ ዓሣና የውኃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል  ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አስቻለው ላቀው ለጎብኝዎች ባደረጉት ገለጻ  ማዕከሉ በአገሪቱ የዓሣ ግብርና ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን እና ሳይንሳዊ እውቀቶች የማሥፋት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ማዕከሉ በአሁኑ ወቅትም  የዓሣ ምርምር እና ልማትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ቴክኒካዊ ሥልጠና እና ድጋፍ ለመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ እየሰጠ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዶ/ር አስቻለው ለልዑካን ቡድኑ እንዳሰረዱት በተለያዩ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የውኃ አካላት ውስጥ የሚጨመሩ ተስማሚ ዓሣ ጫጩቶችን የማራባት ሥራውን አጠናክሮ እንደቀጠለም አስረድተዋል።

የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶ/ር ዮሃንስ ግርማ በበኩላቸው ማዕከሉ እያከናወናቸው ሚገኙ ተግባራት በአገር አቀፍ ደረጃ የዓሣ ዘርፍ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ  የሚኖረው ሚና ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበረው የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ዶ/ር ቶማስ ቸርነት በበኩላቸው እርሳቸው የሚያስተባብሩት ፕሮጀክት በዘርፉ ላይ ለተሰማሩ ተቋማት መጠናከር  የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ የዓሣ  ሀብት  ልማት አስተባባሪ ዶ/ር ፋሲል ዳዊት ኢትዮጵያ በዓመት አንድ መቶ ሺህ ቶን የዓሣ ምርት እተመረተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኃላፊው አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንቅፋት የሆኑትን የዓሣ መኖ እጥረት፣ የዓሣ ጫጩት እጥረት እና የዘመናዊ የዓሣ ማስገሪያ እጥረቶችን ለመፈታት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይ ግብርና ሚኒስቴር የቀየሰው የ10 ዓመት የዓሣ ዘርፍ ልማት ፍኖተ ካርታ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን አሁን ላይ ከሚመረተው ምርት በላቀ ደረጃ ማምረት ያስችላል ብላዋል።

በኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴርና  በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ አማካይኝት በተገኘ ድጋፍ በኢትዮጵያ  ግብርና ሚኒስቴር የሰበታ የዓሣ እርባታ ጣቢያ በ1969 ዓ.ም የግንባታው ስራ ተጠናቆ ስራውን ጀመረ።

ለበርከታ ዓመታት ጣቢያው  የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎችን በሰው ሰራሽ እና በኩሬ  በማባትና በተለየዩ የውኃ አካላት በመጨመር የዓሣ ምርት ለማሳደግ ጥረት ሲያደርግ  ቆይቷል።

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 79/89 በአዲስ መልክ ሲደራጅ ማዕከሉ በአገር አቀፍ የምርምር ድርጅት ሥር እንዲዋቀር ተድርጓል።

ማዕከሉ በአዲስ ሲዋቀርም የብሔራዊ የዓሣ እና የውኃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ተብሎ የሚጠራበትን የአሁኑ ሥያሜውን እንዳገኘ  የማዕከሉ መረጃ ያመለክታል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ በዶ/ር ዮሃንስ ግርማ  የተመራ ልዑካን ቡድን ሰበታ በሚገኘው የብሔራዊ ዓሣና የውኃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ጉብኝት  ላይ በፎቶ ስተይ ።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

error: Content is protected !!