የቦንጋ ግብርና ምርምር በእንስሳት ሃብት ልማት ዙሪያ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለፀ።
ግንቦት 9 – 2013 ዓ/ም – ሰሞኑን የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ የተመራ ልዑክ በከፋ ዞን የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት እና እንስሳት ተዋፅዖ ምርታማነትን ለማሳደግ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን ጉብኝቷል።
የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በተለይ ማህብረሰብ አቀፍ የቦንጋ በግ ዝርያ ማስፋፊያ ስራን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
አሁን ላይም በኢትዮጵያ የበግ ዝርያዎች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው እና በዓይነቱ ልዩ የሆነው የቦንጋ በግ ዝርያን በብዛት ለማስፋፋት የምርምር ማዕከሉ ከፍተኛ ስራ እያከናወነ ነው።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በስፍራው ተገኝተው ባደረጉት ጉብኝት የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል እያከናወነው ያለው ስራ ለሌሎች ማዕከላይ ተመክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
ከቦንጋ በግ ዝርያ ባለፈ የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያ ማስፋፊያ ፕሮጀክትም የተሻለ ተስፋ ሰጭ ሆኗል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ምርትና ምርታማነትን በማስፋት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና በርካታ ወጣቶችም አዳዲስ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን በጉብኝታቸው ላይ አንስተዋል።
ዶክተር ፍቅሩ የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ያገኛቸውን አዳዲስ ዝርያዎች ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከአሁኑ ይበልጥ የተጠናከረ ስራ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
በግብርና ሚኒስቴር በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚደረግለት የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባበሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት በበኩላቸው ፤
እርሳቸው የሞመሩት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በ6 ክልሎች በሚገኙ 58 ወረዳዎች ከ1755 ቀበሌዎች ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግርዋል።
ዶክተር ቶማስ እንዳብራሩት በከፋ ዞን በቦንጋ ግብርና ምርምር የሚሰራው የማህብረሰብ አቀፍ የቦንጋ በግ ዝርያ ማስፋፊያ ፕሮጀክትም የዚህ አንዱ አካል መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ዘለቀ በበኩላቸው ማዕከሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በምርምር ያገኛቸውን ውጤቶች ለህብረተሰቡ ለማድረስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
የዚህ ዘገባ አጠናቃሪ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የማህብረሰብ አቀፍ የቦንጋ በግ ዝርያ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁን ላይ ከትናንት የተሻለ ኑሮ እየኖሩ መሆናቸውን አጋርትዋል፡፡
ተጠቃሚዎች በቀጣይም መንግስት የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ግብርና ሚኒስቴር ይህን መሰል የማህብረሰብ አቀፍ ተጠቃሚነትን የሚያጎላ ፕሮጀክት በሁሉም ክልል ውጤታማ እንዲሆን እስከ ቀበሌ ድረስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።