አርሶ አደሮች በተሻሻለ የበግ ዝርያ እርባታ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

በደቡብ ክልል በእንስሳት ሀብት ዘርፍ በማህበረሰብ ደረጃ ተደራጅተው ላሉ አርሶ አደሮች በእንስሳት እርባታ ስራ አሳታፊ እና ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
በክልሉ እየተተገበረ ባለው የእንስሳት እርባታ ማሻሻዎች ስራ አንዱ ደግሞ ከፋ ዞን ቦንጋ ዙሪያ ወረዳ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ከጥምር ግብርና ሥራ ጎን ለጎን በማህበረሰብ አቀፍ  የተሻሻሉ  የበጎች ዝርያ  እርባታ  ነው፡፡
በጋራ ፍለጎት  የተደራጀው የቦንጋ ማህበረሰብ አቀፍ የበጎች ዝርያ ማሻሻያ ማህበር ከተመሰረተበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ በበግ እርባታ ማሻሻያ ስራ ላይ የተሰማሩት አርሶ አደሮች ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ የበጎች ዝርያ ማሻሻያ ሲመሰረት በጥቂት አርሶ አደሮች ወደ ስራ የገቡ ሲሆን በአሁን ጊዜ 3 መቶ 38 አባላት አለው፡፡ ከዚህ ውስጥ 38 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን የማህበሩ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ሃይሌ አስታውቀዋል፡፡


ሀላፊው ጨምረው እንደተናገሩት ማህበሩ የተመሰረተው ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በግብርና ሚኒስቴር በዓለም በንክ የሚደገፈው  የእንስሳት እና ዓሳ ዘርፍ ሀብት ኘሮጄክት LFSDP ለ/ICARDA/ To International Centre for Agriculture Research and Drought Areas/    ግብረ ሰናይ ድርጅት በሚያደርግው ድጋፍ ነው፡፡ አርሶ አደሮቹን በማህበረሰብ አቀፍ በተሻሻሉ የበጎች ዝርያ ስራ ላይ በማደራጀት በዓመት ከ2 መቶ በላይ የሙከት በጎችን በማደለብ ለሽያጭ ያቀርባሉ፡፡

የቦንጋ ዝርያ በጎች ከሌሎች የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ዝርያ ካላቸው በጎች በምርታማነታቸውና በእድገታቸው የተለዩ ሲሆን  የአንድ የተሻሻለ ዝርያ ያለው የቦንጋ በግ መካከለኛ ክብደት 60 ኪሎ ግራም   ሲሆን  ከፍተኛው ደግሞ ከ 75 ኪሎ ግራም  በላይ እንደሚመዝኑ የማህበሩ ሀላፊ አቶ አለማየሁ አስረድተዋል፡፡
የማህበሩ አባላት በአሁን ጊዜ ከ 1 ሚሊዮን 8 ሺህ 2 መቶ 70 ብር በላይ በባንክ ተቀማጭ ያላቸው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከ250 በላይ  የቦንጋ ሙክት በጎችን ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተገልጸል፡፡

 

በአካባቢው የሚገኘው የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ለአርሶ አደሮቹ እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን በስፍራው ያነጋገርናቸው ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ከሰጡት አስተያየት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት የምርምር ተቋም አንዱ ሲሆን የአካባቢውን አርሶ አደሮች የገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ፤ ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጡ በሽታን  የሚቋቋሙ  የቡና፣ የስንዴ፤ ባቄላ፤ የሙዝ እና የእንስሳት እንዲሁም የማር እና የቦንጋ ምርጥ ዝርያ በጎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ከምርምር ማዕከሉ የተገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

By admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

error: Content is protected !!