የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት የ2013 በጀት ዓመት የፕሮጀክቱን አጠቃላይ አፈፃፀም እና የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት (LFSDP) ከመስከረም 11-13/2014 ዓ.ም. ድረስ በደብረብርሃን ከተማ የ2013 የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዓመታዊ አፈፃፀም ግምገማ ማጠናቀቁን የፕሮጀክቱ ብሔራዊ አስተባባሪ ዶ/ር ቶማስ ቸርነት አስታወቁ፡፡
ዶ/ር ቶማስ ቸርነት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማትፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ቶማስ ቸርነት አጠቃላይ የፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት አፈፃፀም አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ መሰናክሎች ቢያጋጥሙትም በተለይም በክልሎች የነበረውን የተለያዩ ክፍተቶች ተጋፍጦ በርካታ ስራዎችን ለመስራት ተችሏል ብለዋል፡፡
ለዚህም እስከሁን ባለው ሁኔታ በጋራ ፍላጎት ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡት ከተወሰኑ ክልሎች በስተቀር በርካታዎቹ ውጤታማ ስራዎችን እያስመዘገቡ መሆኑን ከሁሉም ክልሎች ከቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡
በዓለም ባንክ የፕሮጀክቱ /Senior Agriculture Economist and Task Team Leader/ የሆኑት አቶ አሳዬ ለገሠ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በቀረበው ሪፖርት መሠረት ፕሮጀክቱ እስከአሁን በተሰሩት በአራቱ እሴት ሰንሰለት በወተት፤ በዶሮ እርባታ፤ በቀይ ሥጋ እና በዓሣ እርባታ ስራዎች ላይ እየታዩ ያሉት ውጤታማ ስራዎች እየተመዘገቡ መምጣታቸው በተለይም በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች የሚያበረታታ መሆኑን አቶ አሳዬ ጠቁመው በአማራ ክልል ፕሮጀክቱ በሚገኝባቸው ወረዳዎች በጦርነት ምክንያት የተጎዱትን እንዴት መልሶ ማቋቋም እንደሚቻል በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር በቀጣይ መልሶ መቋቋም እንዲቻል ጥረት ይደረጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ወደ አርሶአደሮች ወርዳችሁ ስራዎቹን በምትሰሩበት ጊዜ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ራሳችሁን መጠበቅና ህብረተሰቡም መጠንቀቅ እንዳለበት ጨምረው አስረድተዋል፡፡ የእንስሳት እና ዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት በ 6 ክልሎች እና በ58 ወረዳዎች እንዲሁም በ1755 በገጠር ቀበሌዎች በአራቱም የእንስሳት እሴት ሰንሰለት ላይ ከተደራጁት 1560 ሲአይጂ ውስጥ በወተት 2650፣ በዶሮ እርባታ 2123፣ በቀይ ስጋ 5553፣ በዓሣ ሀብት ልማት 234 አርሶ አደሮች እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶች ከእንስሳት ምርት እና ምርታማነት በአሁን ጊዜ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ከፕሮጀክቱ የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡